አሶሳ፣ የካቲት 01/2016 ዓ.ም) የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፉ የተቀናጀ፣ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ በማድረስ የክልሉ ሠላም እና ልማት እንዲጠናከር በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ጸሐይ ሞርካ ገለጹ።
የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በወቅታዊ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ሥራዎች ዙሪያ ከክልሉ ሴክተር መ/ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች እና ከሚዲያ አካላት ጋር ምክክር አድርጓል።
በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የማኅበራዊ ዘርፍ አማካሪ አቶ ጌታቸው ፊሊጶስ፣ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ ወቅታዊ እና ትክክለኛ አጀንዳዎችን ለህብረተሰቡ ቀድሞ የማድረስ ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለበት ጠቁመው፣ ይህም በሀሰተኛ መረጃዎች ስርጭት የሚደርሰውን ጉዳት ያስወግዳል ብለዋል።
ለሕዝቡ የሚደርሱ ወቅታዊ እና ትክክለኛ መረጃዎች መንግስት የሕዝቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ለሚያደርገው ጥረት ስኬታማነት የጎላ ፋይዳ እንዳለውም ገልጸዋል።
ሀገራዊ እና ክልላዊ ወቅታዊ መረጃዎችን ቀድሞ ለህብረተሰቡ በማድረስ ሀሰተኛ መረጃዎችን ቦታ ማሳጣት ከዘርፉ እንደሚጠበቅም አቶ ጌታቸው ተናግረዋል።
የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ አስፋው ወርቁ፣ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሥራዎቻችን የተናበቡ እና ወጥነት ያላቸው መሆን ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ዘመናዊ አሠራሮችን በመጠቀም በተቀናጀ መልኩ ለሀገራዊ አንድነት መጠናከር እና ለህዝቦች መልካም እሴቶች መጎልበት በትኩረት መሥራት እንደሚገባም ጠቅሰው፣ ይህም ለዘላቂ ሠላም እና ለልማት ሥራዎች መጠናከርና ውጤታማነት የጎላ ፋይዳ እንዳለው አስረድተዋል።
የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ጸሐይ ሞርካ፣ ቢሮው በሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ ያለው ግንኙነት እንዲጠናከርና በዘርፉ የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፉ የተቀናጀ፣ ትክክለኛ፣ ወቅታዊና የተናበበ መረጃን ለህብረተሰቡ በማድረስ የክልሉ ሠላም እና ልማት የበለጠ እንዲጠናከር በትኩረት ሊሠራ ይገባል ብለዋል።
በተለይም በአሁኑ ወቅት በማኅበራዊ ሚዲያው ሀሰተኛ እና የተዛቡ መረጃዎች አየተበራከቱ መምጣታቸውን የጠቀሱት ወ/ሮ ጸሐይ፣ ለዚህ ሁነኛ መፍትሔው የተቀናጀ እና የተናበበ መረጃን ለህብረተሰቡ በወቅቱ ማድረስ መሆኑን ጠቁመዋል።
የዘርፉ አካላት መንግሥት የሚያከናውናቸውን ሁለተንተናዊ ሥራዎች በወቅቱ ለህብረተሰቡ በማድረስ ህብረተሰቡ በሠላምና በልማት ላይ በባለቤትነት እንዲሳተፍ የሚያደርጉ ሥራዎችን እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል።
ቢሮው ለሀገርና ለክልሉ ሠላም፣ ልማትና አብሮነት መጠናከር የሚሠራ የተቀናጀ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ሥራ እንዲኖር የጀመረውን ክትትል፣ ድጋፍና ግምገማ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ወ/ሮ ጸሐይ አክለውም፣ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ዘርፉ በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ መሥራት እንደሚገባም አስረድተዋል።
የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፣ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ሥራ የተቀናጀ ጥረት የሚጠይቅ መሆኑን ጠቁመው፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ በክልሉ የተቀናጀ የመረጃ ሥርጭት እንዲኖር የጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ገልጸል።





All reactions:
66
