(አሶሳ፣ ጥር 02/2016 ዓ.ም) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ካቢኔ ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ አጀንዳዎች ዙሪያ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።
ካቢኔው ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ፣ በክልሉ በመንግስት ካፒታል በጀት እና በዘላቂ የልማት ግቦች (SDG) እየተሠሩ የሚገኙ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ያለበትን ደረጃ ገምግሟል።
በክልሉ በመንግስት ካፒታል በጀት እና በዘላቂ የልማት ግቦች (SDG) እየተሰሩ ከሚገኙ ፕሮጀክቶች ውስጥ የዲዛይን ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው ፕሮጀክቶች በሚመለከተው አካል ጥራቱን የጠበቀ ማሻሻያ ተደርጎ በአጭር ጊዜ እንዲቀርቡ፣ የሚደረጉ ማሻሻያዎችን ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ በቅንጅት በመስራት የቅርብ ድጋፍ እና ክትትል ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አቅጣጫ አስቀምጧል።
በክልሉ በመደበኛ ካፒታል በጀት የሚሰሩ ፕሮጀክቶችን እና በዘላቂ የልማት ግቦች ማሳኪያ (SDG) በጀት የሚሰሩ ፕሮጀክቶችን የ5 ወራት የፋይናንስ አፈፃፀም በመገምገም የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችንና ውሳኔዎችን አስቀምጧል።
በሁለተኛ አጀንዳው ክልላዊ የገቢ አሰባሰብ ሂደትና አፈጻጸም ያለበትን ደረጃም ገምግሟል። ባለፉት 6 ወራት ክልላዊ የገቢ አፈፃፀሙ የተሻለ ቢሆንም በቀሪዎች ጊዜያቶች የተለያዩ የገቢ አማራጮችን ማፈላለግ እና አቅምን አሟጦ መስራት እንደሚገባም ካብኔው ተወያይቷል።
የክልሉን የገቢ አሰባሰብን የበለጠ ለማሳደግ ኢንቨስትመንት ዘርፉን በማሳደግ መሬት ወስደው ወደስራ ያልገቡ ባለሃብቶችን ወደ ስራ በማስገባት መክፈል ያለባቸውን ግብር በማስከፈል የገቢ አሰባሰቡን ማሳደግ እንደሚገባ ውሳኔ አሳልፏል።
በተጨማሪም ካቢኔው፣ መደበኛ የበጀት አጠቃቀምን ተመለከተ ሲሆን፣ የሚበጀተውን ውስን የህዝብና የመንግስት ሀብት ከተለመደው የበጀት አጠቃቀም በመውጣት ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ በዕቅድ መሠረት አጣጥሞ መጠቀም እንደሚገባም ተወያይቶ አቅጣጫ ማስቀመጡን የክልሉ ኮሚኒኬሽን መረጃ ያሳያል።
